Micah 7

የእስራኤል መከራ

1ለእኔ ወዮልኝ!
የወይን ዕርሻ በሚቃረምበት ጊዜ፣
የበጋ ፍራፍሬ እንደሚለቅም ሰው ሆኛለሁ፤
የሚበላ የወይን ዘለላ የለም፤
የምንጓጓለት፣ ቶሎ የሚደርሰው በለስም አልተገኘም።
2ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ከምድር ጠፍቷል፤
አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፤
ሰው ሁሉ ደም ለማፍሰስ ያደባል፤
እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል።
3እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤
ገዥው እጅ መንሻ ይፈልጋል፤
ፈራጁ ጕቦ ይቀበላል፤
ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤
ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ።
4ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣
እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት ነው፤
የጠባቂዎቻችሁ ቀን ደርሷል፤
የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መጥቷል፤
የሚሸበሩበትም ጊዜ አሁን ደርሷል።
5ባልንጀራህን አትመን፤
በጓደኛህም አትታመን፤
በዕቅፍህ ለምትተኛዋ እንኳ፣
ስለምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ።
6ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤
ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፣
ምራት በዐማቷ ላይ ትነሣለች፤
የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ ናቸውና።

7እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤
አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ፤
አምላኬ ይሰማኛል።

እስራኤል ትነሣለች

8ጠላቴ ሆይ፤ በእኔ ላይ በደረሰው ደስ አይበልሽ!
ብወድቅም እንኳ እነሣለሁ፤
በጨለማ ብቀመጥ እንኳ፣
እግዚአብሔር ብርሃኔ ይሆናል።
9እርሱን ስለ በደልሁ፣
እስኪቆምልኝ
እስኪፈርድልኝም ድረስ፣
የእግዚአብሔርን ቍጣ እቀበላለሁ፤
እርሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል፤
እኔም ጽድቁን አያለሁ።
10ጠላቴም ታያለች፤
ኀፍረትንም ትከናነባለች፤
“አምላክህ እግዚአብሔር የት አለ?”
ያለችኝን፣
ዐይኖቼ ውድቀቷን ያያሉ፤
አሁንም እንኳ፣
እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች።

11ቅጥሮቻችሁን የምትሠሩበት፣
ድንበራችሁንም የምታሰፉበት ቀን ይመጣል።
12በዚያ ቀን ሰዎች፣
ከአሦር እስከ ግብፅ ከተሞች፣
ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ፣
ከባሕር ወደ ባሕር፣
ከተራራ ወደ ተራራ ወደ እናንተ ይመጣሉ።
13ከሥራቸው የተነሣ፣
በነዋሪዎቿ ምክንያት ምድር ባድማ ትሆናለች።

ጸሎትና ውዳሴ

14ብቻቸውን በዱር ውስጥ፣
በለመለመ መስክ
ወይም በቀርሜሎስ መካከል
የሚኖሩትን፣
የርስትህ መንጋ የሆኑትን፣
ሕዝብህን በበትርህ ጠብቅ፤
እንደ ቀድሞው ዘመን፣
በባሳንና በገለዓድ ይሰማሩ።

15“ከግብፅ እንደ ወጣህበት ዘመን ሁሉ፣
ታምራቴን አሳያቸዋለሁ።”

16አሕዛብ ያያሉ፣ ያፍራሉም፤
ኀይላቸውን ሁሉ ያጣሉ፤
አፋቸውን በእጃቸው ይይዛሉ፤
ጆሯቸውም ትደነቍራለች።
17በደረታቸው እንደሚሳቡ ፍጥረታት፣
እንደ እባብም ትቢያ ይልሳሉ፤
ከዋሻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ፤
በፍርሀትም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤
እናንተንም ይፈራሉ።
18የርስቱን ትሩፍ
ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር
እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው?
ለዘላለም አትቈጣም፤
ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
19ተመልሰህ ትራራልናለህ፤
ኀጢአታችንን በእግርህ ትረግጣለህ፤
በደላችንንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለህ።
20ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ
ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል እንደ ገባህላቸው፣
ለያዕቆብ ታማኝነትን፣
ለአብርሃምም ምሕረትን ታደርጋለህ።
Copyright information for AmhNASV